ልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ አጋር ኢንዱስትሪዎችን የዕውቅና የምስክር ወረቀት ሰጠ።
ልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ፣ በ2017 ዓ.ም. የትብብር ሥልጠና ፕሮግራም ተማሪዎቹን ተቀብለው ላሰለጠኑ አጋር ኢንዱስትሪዎች የዕውቅና የምስክር ወረቀት ሰጠ።
የዕውቅና ፕሮግራሙ ዋነኛ ዓላማ፣ ኢንዱስትሪዎቹ ተማሪዎች በንድፈ-ሀሳብ የቀሰሙትን እውቀት ከተግባር ጋር እንዲያገናኙ በማድረግ ብቁ ባለሙያ እንዲሆኑ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና ማቅረብ ነው። በመድረኩ ላይ እንደተገለጸው፣ የኢንዱስትሪዎቹ ተሳትፎ የትምህርት ሥርዓቱ ዋልታ እንደሆነና ለዚህ ላሳዩት ቁርጠኝነት ኮሌጁ ከፍተኛ ምስጋና እንዳለው ተገልጿል።
የዕውቅና የምስክር ወረቀቶቹም ለኢንዱስትሪዎቹ ተወካዮች በኮሌጁ የስልጠና እና አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ዲን በአቶ እንድሪስ መሐመድ እጅ ተበርክቶላቸዋል።
ከዕውቅና ሥነ-ሥርዓቱ ጎን ለጎን በተካሄደው የግምገማ መድረክ የ2018 ዓ.ም. የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም በዝርዝር ታይቷል። በግምገማው ወቅት የተገኙ ጠንካራ ጎኖች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
የተሸላሚ ኢንዱስትሪዎች ተወካዮች በበኩላቸው፣ ከኮሌጁ ጋር መስራታቸው ብቁ የሰው ኃይልን ለማፍራት ከማገዙም በላይ ለራሳቸውም ተቋማት የወደፊት ሰራተኞችን ለማግኘት እድል እንደሚፈጥርላቸው ገልጸው፣ በቀጣይም ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።



.