Home "ደህንነቱ የተጠበቀ እና ምቹ የስልጠና ከባቢ ለሴት ሰልጣኞቻችን ስኬት!" - የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ "Female Wellness Center"ን በይፋ አስተዋወቀ

"ደህንነቱ የተጠበቀ እና ምቹ የስልጠና ከባቢ ለሴት ሰልጣኞቻችን ስኬት!" - የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ "Female Wellness Center"ን በይፋ አስተዋወቀ

16th July, 2026

የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ ለመላው የተቋሙ ማህበረሰብ አባላት በሥርዓተ-ፆታ እኩልነት፣ አካትቶኝነት እና ደህንነት ዙሪያ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠቱን አስታወቀ።

ስልጠናው በዋናነት ትኩረቱን ያደረገው በኮሌጁ ቅጥር ግቢ ውስጥ በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ስራ በጀመረው "Female Wellness Center" (የሴቶች ደህንነት እና ጤና ማዕከል) ዓላማ፣ አስፈላጊነት እና ተደራሽነት ዙሪያ ላይ መሆኑ ተገልጿል።

በመድረኩ ላይ እንደተመላከተው፤ የስልጠናው ዋነኛ ግቦች በቴክኒክና ሙያ (TVET) ዘርፍ በተለይም በማኑፋክቸሪንግ ስልጠናዎች ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ፣ በአዲስ የተደራጀው ማዕከል የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ማስተዋወቅ እና በግቢ ውስጥ ያሉ ማንኛውንም አይነት የስነ-ልቦና ጫናዎችንና ትንኮሳዎችን በጋራ መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ግንዛቤ መፍጠር ነው።

ይህ በኮሌጁ የተቋቋመው ማዕከል ለሴት ሰልጣኞች ከፍ ያለ ፋይዳ እንዳለው የተገለጸ ሲሆን፣ በተለይም የሚከተሉትን ወሳኝ ጥቅሞች ያበረክታል ተብሏል፦

ደህንነቱ የተጠበቀ ከባቢ (Safe Space)፦ ሰልጣኞች ያለ ምንም ስጋትና ጫና ተግባራዊ ልምምዳቸውን (Practical training) በነጻነት እንዲከታተሉ የስነ-ልቦና እና የሞራል ድጋፍ ይሰጣል።

የጤና እና የንፅህና አጠባበቅ ድጋፍ፦ ለሴት ሰልጣኞች አስፈላጊ የሆኑ የተፈጥሮ ጤና አጠባበቅ ፍላጎቶችንና ቁሳቁሶችን በማሟላት፣ በወቅታዊ ምክንያቶች ከክፍል የመቅረት ሁኔታን ሙሉ በሙሉ ያስቀራል።

የማማከር አገልግሎት (Mentorship & Counseling)፦ ሰልጣኞች በሙያቸው ብቁና በራሳቸው የሚተማመኑ ባለሙያዎች እንዲሆኑ የክህሎት እና የሙያ መመሪያ ይሰጣል።

የኮሌጁ አመራሮች በበኩላቸው፤ ማዕከሉ መቋቋሙ ኮሌጁ ለስርዓተ-ፆታ እኩልነትና ለሁሉን አቀፍ እድገት የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው፣ ማዕከሉ ዘላቂና ውጤታማ አገልግሎት እንዲሰጥ መላው የኮሌጁ ማህበረሰብ የበኩሉን እገዛና ጥበቃ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

.

Copyright © All rights reserved.

Created with