የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ "ተስፋን እንትከል" (Let's Plant Hope) በሚል አነቃቂ መሪ ቃል ከልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 አስተዳደር ጋር በመቀናጀት በአጠቃላይ 1590 የተለያዩ ችግኞችን በግቢ ውስጥና ከግቢ ውጪ ተከለ።
ሀገራዊ ጥሪን በተቀበለው በዚህ የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ላይ፤ የወረዳ 3 ዋና ስራ አስፈፃሚ፣ የደንብ ማስከበር አባላት፣ ልዩ ልዩ ባለሙያዎች እንዲሁም የኮሌጁ ከፍተኛ አመራሮች፣ አሰልጣኞች እና የአስተዳደር ሰራተኞች በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት እና መነሳሳት በጋራ ተሳትፈዋል።
በዕለቱ ከተተከሉት አጠቃላይ 1590 ችግኞች ውስጥ፤ 250 የፍራፍሬ፣ 1,340 የውበት እና የጥላ ዛፎች ይገኙበታል። ኮሌጁ የተቋሙንና የአካባቢውን ስነ-ምህዳራዊ ውበት ለመጠበቅ ካለው ዓላማ አኳያ፣ ከእነዚህ ችግኞች መካከል 890 የሚሆኑትን በኮሌጁ ግቢ ውስጥ የተከለ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 700 ችግኞች ደግሞ ከኮሌጁ ግቢ ውጪ ባሉ የአካባቢው ስፍራዎች ላይ መተከላቸው ተገልጿል።
በችግኝ ተከላ መድረኩ ላይ እንደተብራራው፤ "ተስፋን እንትከል" የሚለው መሪ ቃል ዛሬ በግቢ ውስጥም ሆነ ከግቢ ውጪ የምንተክለው እያንዳንዱ ችግኝ ለነገው ትውልድ ንጹህ አየር፣ ለምለም ምድር እና የተሻለች ኢትዮጵያን ለማስረከብ ያለንን ተስፋና ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
የኮሌጁ ማህበረሰብ እና የወረዳው አስተዳደር ችግኞችን ከመትከል ባለፈ፣ የተተከሉትን ችግኞች በጋራ በመንከባከብ እና በማሳደግ ረገድ የጀመሩትን ኃላፊነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
ይህ የጋራ እንቅስቃሴ፤ የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ ከቴክኒክና ሙያ ስልጠና አሰጣጥ ጎን ለጎን ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ለአካባቢ ጥበቃ እና ለሀገራዊ የአረንጓዴ ልማት እያበረከተ ያለውን ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያሳይ መሆኑ ተመላክቷል።




.