የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የ2018 በጀት ዓመት የማጠቃለያ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ አካሄደ።
በግምገማ መድረኩ ላይ የኮሌጁ ዋና ዲን አቶ ተኩ ታዬ የ12 ወራቱን ዝርዝር አፈጻጸም አቅርበዋል። ዲኑ በሪፖርታቸው እንዳመለከቱት፤ ኮሌጁ የትምህርትና ስልጠና ጥራቱን በማረጋገጥ የ"ISO 21001:2025" የትምህርት ተቋማት ማኔጅመንት ሲስተም ሰርቲፊኬት ባለቤት መሆን መቻሉ የዓመቱ ታላቅ ስኬት ነው።
የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት አኳያ፤ በመደበኛው መርሃ ግብር 1 ሺህ 306፣ በክህሎት ላይ በተመሰረተ የአጫጭር ጊዜ ስልጠና ደግሞ 28 ሺህ 785 ዜጎችን ተቀብሎ በማሰልጠን የኢንዱስትሪውን ፍላጎት ለማሟላት ሰፊ ስራ ተሰርቷል። የትብብር ስልጠናን በማስፋትም 94 በመቶ የሚሆኑ የ2017 ተመራቂዎችን ከስራ ጋር ማስተሳሰር (Tracer Study) መቻሉ በሪፖርቱ ተብራርቷል።
በተጨማሪም የኮሌጁ አሰልጣኞች በማኑፋክቸሪንግ፣ በከተማ ግብርና፣ በኮንስትራክሽን እና באገልግሎት ዘርፍ ለተሰማሩ 859 ኢንተርፕራይዞች የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ ሰጥተዋል። አሰራርን ከማዘመን አንጻርም፤ የኦንላይን ምዝገባ፣ የንብረት አያያዝ እና ብሌንዴድ ለርኒንግ (Blended Learning) ስልቶችን ተግባራዊ ማድረጉ ተገልጿል።
ይሁን እንጂ በግምገማው ወቅት፤ በመደበኛው የስልጠና መርሃ-ግብር የሙያ ብቃት ምዘና (COC) የማለፍ ምጣኔን ይበልጥ ማሳደግ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ ተቀምጧል።




.