በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች መካከል የሰልጣኞችን የስነ-ልቦና ደህንነት የሚያረጋገጥ ታሪካዊ ስምምነት ተፈረመ
የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞችን አካዳሚያዊ እና ስነ-ልቦናዊ ጤንነት ለማረጋገጥ እና ድጋፉን ተቋማዊ ለማድረግ የሚያስችል ታሪካዊ የመግባቢያ ስምምነት (MoU) በልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ አስተናጋጅነት ተፈረመ።
ይህ ስትራቴጂካዊ የትብብር ማዕቀፍ የተዘረጋው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልቦና ትምህርት ቤት፣ በጀርመን ተራድኦ ድርጅት (GIZ-QEP II) ፕሮጀክት፣ እንዲሁም በአራት የቴክኒክና ሙያ (TVET) ኮሌጆች (ማለትም አቃቂ ፖሊቴክኒክ፣ አዲስ አበባ ተግባረ-እድ፣ ጎፋ ኢንዱስትሪያል እና ልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጆች) መካከል ነው።
በኮሌጁ ምክትል ዲን ወ/ሮ ትዕግስት ድንቁ አወያይነት በተመራው በዚህ መርሃ-ግብር ላይ እንደተገለጸው፤ የስምምነቱ ዋና አላማ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልቦና ተማሪዎች በነዚህ የሙያ ኮሌጆች ውስጥ የሙያና ስነ-ልቦና ምክር (VGC) ቡድንን በመቀላቀል የተግባር ልምምዳቸውን እንዲያደርጉና ለሰልጣኞች የስነ-ልቦና ድጋፍ አመቻች ሆነው እንዲሰሩ ማድረግ ነው።
የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ ዋና ዲን አቶ ተኩ ታዬ መድረኩን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር፤ "ይህ ስምምነት ሰልጣኞች ስነ-ልቦናዊ መረጋጋት አግኝተው በስልጠናቸው ስኬታማ እንዲሆኑ ትልቅ አቅም ይፈጥራል" በማለት የትብብሩን አስፈላጊነት አብራርተዋል። በGIZ-QEP II የአውሮፓ ህብረት ክፍል ሥራ አስኪያጅ ፍራንዚስካ ሹማን እንዲሁም የፕሮግራም ክፍል አስተዳዳሪው አቶ ብሩክ አምሃ በበኩላቸው፤ ይህ አካዳሚያዊ ትብብር ወጣቶችን ለማብቃት እና በማህበረሰቡ መካከል ማህበራዊ ትስስርን ከመፍጠር አኳያ የጎላ ፋይዳ እንዳለው አስገንዝበዋል።
በመድረኩ ትኩረት ከሳቡት አጀንዳዎች መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልቦና ክፍል ኃላፊ ዶ/ር እንዳልካቸው ተሰራ ስለ አእምሮ ጤና፣ የሰልጣኞችን ስኬት በማሳደግ ረገድ የስነ-ልቦና ድጋፍ (MHPSS) ስላለው ሚና የሰጡት ጥልቅ ማብራሪያ ይገኝበታል። እንዲሁም የVGC ኦፊሰር ወ/ሮ ወይንእሸት መኮንን በኮሌጆች ውስጥ አሁን ላይ ያለውን የVGC የስነ-ልቦና ድጋፍ ልምምድ ተሞክሮ አጋርተዋል።
የመግባቢያ ስምምነቱን ፊርማ ተከትሎም፣ የክብር እንግዶቹ እና ፈራሚ አካላት በልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የተደራጁትን የግለሰብና የቡድን የምክር አገልግሎት ቢሮዎች እንዲሁም "የሴቶች የጤና እና ደህንነት ማዕከልን (Female Wellness Center)" የጎበኙ ሲሆን፣ ኮሌጁ ለሰልጣኞች ደህንነት የሰጠው ትኩረት ከፍተኛ አድናቆትን አትርፏል።
ይህ ታሪካዊ መርሃ-ግብር ለቀጣይ የጋራ ስራዎች መሰረት በጣለ የልምድ ልውውጥ (ኔትወርኪንግ) እና በምሳ ግብዣ በድምቀት ተጠናቋል።




.