እንኳን_ደስ_አላችሁ!
የተከበራችሁ የኮሌጃችን አመራሮች፣ አሰልጣኞች፣ የአስተዳደር ሰራተኞች፣ ሰልጣኞች እና መላው የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ ማህበረሰብ በሙሉ፤
ኮሌጃችን የረጅም ጊዜ ራዕዩን በማሳካት ለትምህርትና ስልጠና ተቋማት በሚሰጠው ዓለም አቀፍ የጥራት መመዘኛ፤ ለ ISO 21001:2025 (Educational Organizations Management System - EOMS) የጥራት ሰርቲፊኬት እውቅና በይፋ የታጨን መሆኑን በደስታ እንገልጻለን።
ይህ ታሪካዊ ስኬት የአንድ ግለሰብ ወይም የስራ ክፍል ብቻ ሳይሆን፤ ሁላችንም እንደ አንድ ቤተሰብ ሆነን ለጥራት፣ ለልህቀት እና ለተቋማችን ዕድገት የከፈልነው የጋራ ጥረት፣ መስዋዕትነት እና የትጋት ፍሬ ነው።
አሰራራችንን ከዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ጋር ለማጣጣም ሌት ተቀን የደከማችሁ አመራሮች፣ የላቀ የሙያ ስነ-ምግባር በማሳየት ስልጠናውን በውጤታማነት የምትመሩ አሰልጣኞች፣ ሂደቱን ያለምንም መስተጓጎል የደገፋችሁ የአስተዳደር ሰራተኞች እና የኮሌጃችን የልፋት ውጤት የሆናችሁ ሰልጣኞቻችን፤ ለዚህ ስኬት ላበረከታችሁት ወደር የለሽ አስተዋጽኦ በኮሌጁ ማኔጅመንት እና በራሴ ስም ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
ለዚህ ዓለም አቀፍ የISO 21001:2025 እውቅና መታጨታችን፤ ኮሌጃችን የሚሰጠው የትምህርትና ስልጠና አገልግሎት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን በተግባር ያረጋገጠበት ነው። ይሁን እንጂ ይህ ድል የጉዟችን መጀመሪያ እንጂ ማብቂያ አይደለም። አሁን የተረጋገጠልንን ዓለም አቀፍ እውቅና አጽንተን በመያዝ፣ የተቋማችንን የአገልግሎት ጥራት ይበልጥ በማሳደግ በየዘርፉ ብቁና ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ኃይል ለማፍራት ከምንጊዜውም በላይ በቁርጠኝነትና በቅንጅት ልንሰራ ይገባል።
በድጋሚ ለዚህ ታላቅ ስኬት እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ደስ አለን!
.