"ቴክኖሎጂ ለአመለካከት ሽግግርና ለኢንዱስትሪ መነቃቃት"፤ የልደታ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የፈጠራ ውጤቶቹን ለእይታ አቀረበ።
🇪🇹አዲስ አበባ | ሚያዝያ 16/ 2018 ዓ.ም🇪🇹
"ቴክኖሎጂ ልህቀት ለአገር ብልጽግና" በሚል መሪ ቃል በመከበር ላይ የሚገኘው 16ኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት አካል የሆነው የቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን፣ በልደታ ማኒፋክቸሪንግ ኮሌጅ በድምቀት ተካሂዷል። ኮሌጁ በማምረቻ፣ በአገልግሎትና በአይሲቲ (ICT) ዘርፎች በአሰልጣኞችና ሰልጣኞች ጥምረት የተፈበረኩ 10 ያህል ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን ለኢንዱስትሪዎች፣ ለኢንተርፕራይዞችና ለአካባቢው ማህበረሰብ ለእይታ አቅርቧል።
የአመለካከት ለውጥ ለዘርፉ ዕድገት - አቶ ተኩ ታዬ
የኮሌጁ ዋና ዲን አቶ ተኩ ታዬ የአውደ-ርዕዩን ፋይዳ አስመልክተው በሰጡት ሰፊ ማብራሪያ፣ እንዲህ ያሉ መድረኮች በኅብረተሰቡ ዘንድ ስለ ቴክኒክና ሙያ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። ዲኑ እንደተናገሩት፣ ምንም እንኳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኅብረተሰቡ አመለካከት እየተሻሻለ ቢመጣም፣ አሁንም ዘርፉን ዝቅ አድርገው የሚመለከቱ "ጫፍ የረገጡ" አመለካከቶች በሚፈለገው ልክ አልተቀየሩም።
"በየዓመቱ እንዲህ ያሉ የቴክኖሎጂ ፈጠራ አውደ-ርዕዮችን የምናዘጋጀው ኅብረተሰቡ በዘርፉ ላይ ያለውን ግንዛቤ እንዲያሰፋና የቴክኒክና ሙያ ትምህርት የብልጽግና መሠረት መሆኑን እንዲገነዘብ ለማድረግ ነው" ብለዋል አቶ ተኩ ታዬ።
አክለውም፣ ቴክኖሎጂዎቹ በሰልጣኞች የተሠሩ መሆናቸውን ኢንዱስትሪዎች ሲረዱ፣ በሰልጣኞቻችን አቅም ላይ ያላቸው እምነት እንዲጨምርና ነገ ለሚጫወቱት ታላቅ ሀገራዊ ሚና መንገድ እንደሚከፍትላቸው ዲኑ በዝርዝር አስረድተዋል።




.